በፋሲል ፀጋዬ

ከሀገር መሪዎች እስከ ባለሙያዎች ጉዳዩን በትክክል ይረዱታል ተብሎ የማይታሠቡ ግለሰቦች ሳይቀር  ስለጋራ መከላከያ (Herd Immunity) ሲናገሩና ሲጽፉ እንሰማለን ፤ እናነባለን፡፡የጋራ መከላከያ (Herd Immunity) ምን ማለት ነው? ለምንስ ለኮቪድ-19 እንደመፍትሔ ሊነሣ ቻለ?

ስለጋራ መከላከያ (Herd Immunity) ከማውራታችን በፊት የሰውነታችን የበሽታ መከለካያ ሥርአት  እንዴት እንደሚሠራ  አብዛኛዎቻችን ልንረዳ በምንችለው መንገድ አስቀድመን ብናይ መልካም ነው፡፡

  • አንድ አይነት በሽታ አምጭ ተህዋስ ወደ ሰውነታችን ሲገባ ሰውነታችን መጀመሪያ የሚያደርገው የገባውን ተህዋስ የራሱ ሴል ወይንም አካል መሆኑንና አለመሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡
  • የራሱ አለመሆኑን ካረጋገጠ በኋላ የገባውን ተህዋስ በመያዝ በተለያዩ ውህዶች ክፍል በክፍል በመበታተን ወደ ሴሎች የሚገባበትን መንገድ እና የሚያጠቃበትን ስልት ያጠናዋል፣ ግልባጩን ያዘጋጃል፡፡
  • የሰዉነታችን መከላከያ ስርዐት ለለያቸው የተህዋሲያኑ መውጊያ ማክሸፊያ ያመርታል፡፡ ይህም በእንግሊዝኛ Antibody ይባላል፡፡   
  • ሰውነታችን ያመረተውን ማምከኛ በብዙ እጥፍ በማባዛት የወራሪውን መውጊያ በመለጎም፣ መገናኛ መስመሩን በመዝጋት ወይም መርዙን በማክሸፍ ከጥቅም ውጭ ለማድረግ ውጊያ ይገጥማል፡፡
  • በዚህ ውጊያ የደም ውስጥ ወይም የሴል አካባቢ በመረበሹና በመመረዙ ምክንያት ሰውነታችን እንደዬ በሽታ አምጭ ተህዋሲያኑ አይነትና ብዛት እንዲሁም የመከላከያ ሀይላችን እንደሚያደርገው ጥረትና ጥንካሬ ሰውነታችን በትኩሳት ይመታል፤ ማንቀጥቀጥ እና ራስ ምታትም ሊኖረው ይችላል፡፡ ውጊያው የሚካሄድበት አካባቢ አንድ የሰውነት ክፍል ከሆነ ወይም ያ ብልት ተግባሩን በአግባቡ እንዲወጣ ከሚረዱት ቅመም ማምረቻዎች አካባቢ ከሆነ የጦር አውድማ የሆነው  የውስጥ አካል/ብልት (Organ) በእጅጉ ይጎዳል ለዚህ ሳንባ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡  
  • የሰውነታችን መከላከያ ከተሳካለት የገባውን ወራሪ ተህዋስ ጠራርጎ ያስወግዳል፡፡ የገባውን እና ሰውነታችን ውስጥ በመራባት ላይ የሚገኘውን ወራሪ ተህዋሲያን የሰውነታችን መከላከያ ሀይል ሙትና ቁስለኛ በሽንት፣ በአክታ፣ በላብና በመሣሰሉት መንገዶች ያስወግዳል፡፡
  • የተመረተው ማምከኛ እንደዬ ተህዋሱ አይነት በሰውነታችን ውስጥ ለአጭር ጊዜ ወይም ለረዥም ጊዜ ሊቆይ ይችላል፡፡
  • ለረዥም ጊዜ የሚቆዩትን ሰውነታችን ኮዱን በማስታወስ ተመሣሣይ ወራሪ በገባ ቁጥር ተህዋሱ ሰውነታችን ተላምዶ በብዛት ከመራባቱ እና ህመም ከማስከተሉ በፊት ተመርቶ የነበረውን መከላከያ በማስታዎስና በማነቃቃት በበሽታው መያዛችንን እንኳን ሳናውቅ ያጠፋዋል፡፡ ይህ የህይወት ዘመን (lifelong immunity) በመባል ይታወቃል፡፡ ጉንፋን፣ ፈንጣጣ፣ የኩፍኝ በሽታ በዚህ የህይወት ዘመን መከላከያ እንዲመረት በማድረግ ይታወቃሉ እንደዚህ ዓይነት ጠንካራ የመከላከያ ምላሽ የሚያከትሉ ተሕዋሲያን (strong immunogenicity) ያላቸው ይባላሉ፡፡
  • እንደ ወባ በሽታ አምጭዎች ያሉት ደግሞ ለጥቂት ቀናት የሚቆይ መከላከያ እንዲመረት ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ነው ወባ ለህመም በመዳረግና በገዳይነቱ የሚታወቅ ቢሆንም መከላከያ ክትባት እስካሁን ያልተገኘለት፡፡
  • አንዳንድ ተህዋሲያን ቶሎ ቶሎ ራሳቸውን ስለሚቀያይሩ ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸው በርካታ በሽታ የሚያስከትሉ በማህበረሰቡ ውስጥ ሊዛመቱ ይችላሉ፡፡ ያንዱ ክትባት ሌላውን ላይከላከል ይችላል፡፡ ለእያንዳንዱ በተለያዩ አካባቢ ወይም በጣምራ ለሚዛመቱ ተህዋስያን ክትባት በተናጠል አምርቶ መክተብ ደግሞ ሂደቱን አስቸጋሪና ውድ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ ድብልቅ (cocktail ) ክትባት ማዘጋጀት ተችሏል፡፡ የተለያዩ የኢንፍሉዌንዛ ዝርያዎች ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡

የጋራ በሽታ መከላከያ (Herd Immunity) ምንድን ነው? በአንድ ህዝብ ውስጥ እንዴት ሊመጣ ይችላል?

  • የጋራ መከላከያ (Herd Immunity) በሰው ሰራሽ ዘዴ (በክትባት) ወይም በተፈጥሮ (በበሽታው ተይዞ በመዳን) ሊመጣ ይችላል
  • የጋራ መከላከያ (Herd Immunity) የአንድን የክትባት መርሀግብር ግብ ለማስቀመጥ ይረዳል፡፡
  •  የጋራ በሽታ መከላከያ (Herd Immunity) በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች በተፈጥሮም ይሁን በክትባት የአንድ በሽታ መከላለከያ በአብዛኛው ሰው ውስጥ በመኖሩ ጥቂት ሰዎች የበሽታው መከላከያ ባይኖራቸውም ወይም ባይከተቡም በበሽታው አይጠቁም ማለት ነው፡፡ በርካታ ሰዎች በሽታዉ ስለማይዛቸውና በሽታው በአካባቢያቸው ከሰው ወደሰው እየተዘዋወረ ስለማይቆይ ለበሽታው የተጋለጡ ወይም መከላከያ የሌላቸው ሰዎችን የማግኘት እድሉ ይቀንሣል፡፡
  •  በጋራ መከላከያ (Herd Immunity) መከላከል የሚቻለው በህብረተሰቡ ውስጥ ተሰባጥረው የሚገኙ ጥቂት ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ነው፡፡

 ከላይ በገለጽነው መሰረታዊ እውቀት መነሻነት የጋራ በሽታ መከላከያ (Herd Immunity) ደረጃ የሚደረሱ በሽታዎች/ ተህዋሲያን ምን አይነት ባህሪ አላቸው?

በተፈጥሮ / በበሽታው በመያዝ/ infection

  • በሽታው በአብዛኛው ሰዎች ላይ የከፋ ህመም  ወይም ሞት የማያስከትል ቀለል ያለ በሽታ መሆን አለበት፡፡
  • በሽታ አምጭው ተህዋስ ከሰው ወደ ሰው ብቻ የሚተላለፍ መሆን አለበት ወይም ከሌሎች እንስሳትም ሆነ ከአካባቢ የማይገኝ መሆን አለበት (No animal reservoir or no environmental source).  
  • የበሽታው ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ፍጥነት ዝግ ያለ መሆን አለበት (medium/low contagious).
  • ቶሎ ቶሎ ራሱን የማይለውጥ/ተመሣሣይ በሽታ የሚያስከትሉ የተለያዩ ዝርያ የሌሉት መሆን አለበት፡፡
  • ረዘም ላለ ጊዜ በሰውነት ውስጥ መቆየት የሚችል የመከላከያ ሀይል እንዲመረት የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡

በሰው ሰራሽ ዘዴ/ በክትባት  

  • በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል ደህንነቱ የተረጋገጠ ክትባት ያለውና በበቂ መጠን የተመረተ/ማምረት የሚያስችል አቅም ያለው መሆን አለበት፡፡
  • አብዛኛውን ህዝብ ለመከተብ የሚያስችል የተደራጀ ተደራሽና ተቀባይነት ያለው የክትባት ስርዓት መኖር አለበት
  • በአብዛኛው 80 ከመቶው በላይ የሚሆነውን ነዋሪ ወይም መከተብ ያለበትን የህብረተሰብ ክፍል መሸፈን የሚያስችል መሆን አለበት፡፡
  • ክትባቱ ከተሰጠ በኋላ ለረዥም ጊዜ በሸታውን ለመከላከል የሚችል መሆን አለበት፡፡
  • ክትባት ቢከተቡም ባይከተቡም ለበሽታው በልዩ ሁኔታ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በህዝቡ ውስጥ ተሰራጭተው የሚገኙ መሆን አለባቸው ወይም በአንድ አካባቢ ተለይተው የማይገኙ መሆን ይኖርባቸዋል (randomly distributed in the community).

በልዩ ሁኔታ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚባሉት

  1. በተፈጥሮ የበሽታ መከላከያ ማምረት የማይችሉ ሰዎች
  2. ያልዳበረ የበሽታ መከላከያ ያላቸው ህፃናት፣ የተዳከመ የበሽታ መከላከያ ስርዓት ያላቸው አረጋውያን
  3. ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝ ሰዎችና የፀረ ኤች አይ ቪ መድሀኒት የማይወስዱ/ያልጀመሩ ሰዎች
  4. የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ሰዎች
  5. የበሽታ መከላከል አቅማቸው ሆን ተብሎ እንዲዳከም የተደረገ ሰዎች ወይም የበሽታ መከላከያ ስርዓትን የሚያዳክም መድሀኒት የሚወስዱ ሰዎች (የካንሰር ህክምና የሚወስዱ፣ የአካል ንቅለ-ተከላ የተደረገላቸው)
  6. ዘላቂ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች (የደም ግፊት፤ የስኳር ህመም ፣ ካንሰር በሽታ)
  7. ሲጋራ የሚያጨሱና የተለያዩ አነቃቂ ንጥረነገሮችን የሚወስዱ ሰዎች ናቸው

 ብዙዎች እንዳወሩለት የጋራ መከላከያ (Herd Immunity) ኮቪድ-19 ለመከላከል እንደ ስልት መቆጠሩ አግባብ ነው?

  • ኮቪድ-19 በርካታ ሰዎችን ለከፋ ህመምና ሞት የሚዳርግ በሽታ ነው /የጋራ መከላከያ ከመድረሱና በሽታው ከመጥፋቱ በፊት በርካታ ሰዎችን ይጎዳል በጣሊያን በስፔንና በአሜሪካ እንዳየነው ሆስፒታሎችና የጤና ስርዓቱ ከአቅማቸው በላይ ይሆናል፡፡
  • ኮቪድ-19 ከሰው ወደሰው የመተላለፍ ሂደቱ ፈጣን ነው፡፡
  • ኮቪድ-19 እስካሁን የተረጋገጠ የመከላከያ ክትባት አልተገኘለትም ብቻ ሳይሆን ታመው የዳኑ ሰዎች በድጋሚ እንደማይያዙ አልተረጋገጠም ፡፡
  • እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት ኮቪድ-19 መጀመሪያ በተፈጥሮ ከሚኖርበት ከሌሊት ወፍ ከዚያ ፓንጎሊን ወደተባለው እንሥሣ በመዛመትና ብሎም ወደ ሰው በድንገት ከገባ በኋላ ሰውን ተላምዶ ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ ጀመረ ነው የሚባለው፣ በኒዎርክ የእንሰሳት ማቆያ ውስጥ የሚገኙ ነብሮች በቤልጂዬም ባለቤቷ በኮቪድ-19 የተያዘባት ድመት በሽታው ተገኝቶባቸዋል፡፡

ስለዚህ ከላይ በተዘረዘሩት መመዘኛዎች መሠረት የጋራ መከላከያ (Herd Immunity) ለኮቪድ-19 መከላከያነት እንደስልት ሊወሰድ አይገባውም እንላለን ፡፡

    ከመቶ አስር ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለሚኖርባት ኢትዮጵያ ፣ ገና ዳዴ የሚል የህክምና አገልግሎት ላላት ሀገር የጋራ መከላከያ (Herd Immunity) ኮቪድ-19ን ለመከላከል እንደሚረዳ አስመስሎ ማቅረብ ታዲያ ምን ማለት ነው?

  • የጋራ መከላከያ (Herd Immunity) እንዲሠራ በትንሹ ከ 60 – 80% /በመቶው የሚሆን ህዝብ በበሽታው መያዝ አለበት ይህ ማለት 88 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ማለት ነው ስለዚህ በ Herd Immunity ለመከላከል የሚደከመው ለቀሪው ሀያ በመቶው ለሚሆነው ህዝብ ነው፡፡  
  • በበሽታው ከታያዙት ውስጥ 15 በመቶው በሚሆኑት ላይ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልገው የከፋ ህመም ያስከትላል፡፡ 13.2 ሚሊዮን ሰው ማለት ነው፡፡
  • ከእነዚህ ውስጥ ከ3 እስከ 5 በመቶው የጽኑ ህመም ህክምና ያስፈልጋቸዋል ብሎም ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉ ከስድስት መቶ ሽህ ህዝብ በላይ ማለት ነው፡፡ የጋራ መከላከያ (Herd Immunity) እንደሚሰራ ለመሞከር እና ጥቂቶችን ለመከላከል ሲባል ይህን ያህል መሰዋዕትነት መክፍል የሚሻ ህዝብና መንግስትስ እንዲሁም ይህን ጽንሰ ሀሣብ  ለመተግበር ሚፈቅድ ባለሙያ በምድር ላይ ይኖር ይሆን?

ትባት መድሀኒት ሳይሆን ሰውነታችን ለገባው ባዕድ ተህዋስ መከላከያ እንዲያመርት የሚያነቃቃ በሽታ የማያስከትል (የተዳከመ/ የተሕዋሱ የተወሰነ ክፍል/ መርዛማነቱ የቀነሰ ወይም በምትኩ ከበሽታ አምጭው ጋር ተመሳስሎ የተዘጋጀ) ሰው ሰራሽ ውህድ ነው፡፡ አብዛኛው ክትባት በአፍ ወይም በመርፌ ይሰጣል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may also like

No announcement available or all announcement expired.