የመፀዳጃ ቤት ቅርጫቶች የአኗኗራችን ሌላው ገመና !

በዚህ ጉዳይ መፃፍ እጅግ ያሣፍራል፣ ሆኖም ትንሽ የሚመስሉ በዓለም ፊት የሚያሳንሱን ገመናችን ማን ይንገረን ፣ መቼ ነው ነውር የሆኑ ልማዶቻችን ተወያይተን የምንቀይራቸው፡፡መቼም የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀምና አያያዝ እንደ ሕዝብ በጋራ የሚያስተቸን ፣ የሚያስነውረንና የሚያስንቀን ግዙፍ ችግራችን ነው፡፡ የየቤቱን ቤቱ ይቁጠረውና በየመስሪያ ቤቱ እከሌ ገብቷል መጸዳጃ ቤቱ ገምቷል የሚባሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ከጅምሩ ለመጸዳጃ ቤት የሚሠጠው ግምት እጅግ የወረደ ከመሆኑ የተነሳ የሆነ ስርጥ ሲገኝ እነደነገሩ ሸጎጥ ይደረጋል፡፡

በዚህ ረገድ አንድ ኬንያዊ የሥራ ባልደረባዬ ለመስክ ስራ ወደ ክፍለ ሀገር ሄደን ለምሣ በተቀመጥንበት ወቅት ያለንን አልረሣውም፡- “ኢትዮጵያ ውስጥ መጸዳጃ ቤት የት ነው ብለህ መጠየቅ አይጠበቅብህም አንድ ቆሸሸ ያለ ጥግ ካየህ ወደዛ መሄድ ነው ብትሳሳትም ኩሽና ሆኖ ታገኘዋለህ እልፍ ስትል ደግሞ መጸዳጃ ቤቱን፣ ሁለቱ በምንም ሁኔታ አይተጣጡም ለዛ ነው መሠል መጸዳጃ ቤት የሚል አመልካች ጽሁፍ ያልተለመደው” ነበር ያለን፡፡

 አንዴ ደግሞ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴተር በምሠራበት ጌዜ እንዲህ ሆነ፡- አንድ ትላልቅ የግሎባል ፈንድ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተተ ቡድን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ሥራ ለመገምገምና በወቅቱ ያሸነፍነውን ተጨማሪ ስምምነት ለመፈራረም ወደ ሀገራችን መጥቶ ስለነበር በወቅቱ የሚኒስቴር ዲኤታ ቢሮ ውስጥ ስብሰባ እየተካሄደ ነበር፡፡ የወቅቱ የግሎባል ፈንድ ትልቅ የሥራ ኃላፊ የሆኑ አንድ ምዕራባዊ ከኔ አጠገብ ተቀምጠው ነበርና መጸዳጃ ቤት መሄድ እንደሚፈልጉ ጠየቁኝ ሁኔታውን ስለማውቅ እየተሳቀቅሁ ካጠገባቸን ውሃ በማቅረብ ላይ ለነበረችው የሚኒሰተቴር ዲኤታው ፀኃፊ በምልክት ነገርኳት፡፡ በቅርብ ርቅት ከነበረ መሣቢያ ቁልፍ አውጥታ ስትሠጠው ሰውየው ግራ እንደተጋባ ተቀበላት፤ ከዛም መጸዳጃ ቤቱን አመለከተቸውና ወደዚያው ሄደ፡፡

ከበርካታ ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ነጭ ፊቱ ቲማቲም መስሎና ኮቱን በእጁ አንጠልጠሎ ወደ ቦታው ሲመለስ ጎኔን በክርኑ ጎሸም አድርጎ ፡- “ታውቃለህ መፀዳጃ ቤቱ ውስጥ ምንም ሶፍት አልነበረም ውኃም የለም ምን ማድረግ ነበረብኝ፡፡ እኔ ስላጣደፈኝና እንዲህ ይሆናል ብዬ ስላልገመትኩ አለመኖሩን አላስተዋልኩም እነደገባሁ ነበር የተቀመጥኩበት አለኝና ካልሲ የሌለው የግራ እግሩን ገለጥ አድርጎ አሣየኝ በድንጋጤ አፌ ተለጉሞ ቀረ፣ ከኔ መልስ ሣይጠብቅ አሁንም በሹክሹክታ ቀጠለ ስለተጣደፍኩ አላየሁትም ነበር እንጅ መጸዳጃ ቤቱ ሲጀመር ቆሻሻ ነበር፣ ከጎኔ ቅርጫት ሙሉ የሰው አይነምድር አየሁ፣ የኮት መስቀያ ስላልነበረው ታቅፌ የያዝኩት ኮት እጅ ቅርጫቱ ውስጥ እስከ ግማሽ ገብቶ ሳገኘው መቋቋም አቅቶኝ አስታወከኝ” አለና ፊቱን አዞረ:: እኔስ ምን መልሥ ይኖረኛል ከሀፍረት በስተቀር፡፡

ከዛ በኃላ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች በኩራት የሚያቀርቡትን ይህን አከናወንን ይህን አቀድን ሪፖርት የሰማ አይመስለኝም ምንም አስተያየት ሳይሠጥ ቆይቶ በሻሂ እረፍት ጊዜ ምቾት አልተሠማኝም ብሎ ወደ ሆቴሉ ተመለሠ፡፡ ከዚያን ግዜ ጀምሮ ይህን ሰው በማንኛውም ዓለም አቀፍ ስብሰባ ባየሁት ቁጥር እንዳያገኘኝ ስሸሸው እኖራለሁ፡፡ እንግዲህ በዚህ ሠው አእምሮ የተሳለችውን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አስቧቸው፡፡

በየመስሪያ ቤቱ ሶፍትና ሳሙና ይሰጣል:: ቢያንስ የጤና ጥበቃን አውቅ ነበር ታዲያ ለምንድ ነው በየመጸዳጃ ቤቱ ሶፍትና ሳሙና የማይቀመጠው፣ ለምንስ ለያንዳንዱ ሠራተኛ ይታደላል፡፡ የጽዳት ሠራቶኞች ኃላፊነት ሆኖ ሲያልቅ እየተኩ ለሁሉም አገልግሎት ላይ ቢውል አይሻልም ነበር፡፡

በሌላ መልኩ የመጸዳጃ ቤት መቀመጫዎች መሰባበርና መቆሸሽ ሳያንስ ከጎን ባይነምድር ቅሬት በተኳሉ ሶፍትና ወረቀት የተሞሉ ቅርጫቶች ይገኛሉ፡፡ ይህ እጅግ አስቀያሚ ልማድ በድንጋይ ዘመን የተጀመረ ይመስለኛል፡፡

አብኣኛው የከተሜ ነዋሪ በየተፋሰሱ ከመጸዳዳት ተላቆ በየጓሮው ጉድጓድ ቆፍሮ መፀዳዳት ሲጅምር ከግቢ ጠጠርና ድንጋይ ለቅሞ ነበር የሚጠቀመው፣ ወረቀትና ሶፍት እንደልብ አይገኝምነበርና፤ ቢገኝም የመጠቀም በህሉ አልዳበረም ስለዚህ ጉድጓዱ በድንጋይ እነዳይሞላ ያለው አማራጭ ከጠረጉበት በኃላ ዘወር ወዳለ ቦታ ወይም በቅርጫት ማጠራቀም የተሻለው ዘዴ ነበር አሁን ዘመን ተቀይሮ የመጸዳጃ ቤቱ አይነት ተለውጦ ለምነድነው ጥቅም ላይ የዋለ ሶፍትና ወረቀት ባስቀያሚ ሁኔታ በቅርጫት ውስጥ የሚጠራቀመው? ሲጀመር ሶፍት የተሠራው እርጥበት ሲነካው በቀላሉ እነዲበታተን ታስቦ ነው በምንም ዓይነት ሁኔታ መጸዳጃ ቤት ሊደፍን ወይም ሊሞላ አይችልም፡፡

ባይሆን ቅርጫቱን ቦታ ሲግኝ ለመጣል በኪሣችን ያስቀመጥነውን ፕላስቲክ ነክ የሆኑና ሌሎች ደረቅ ቆሻሻ እነዲሁም የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ/ሞዴስ ማሶገጃነት ብንጠቀምበት ያሳምናል፡፡ ያም ቢሆን ከእጅ መታጠቢያ አካባቢ እንጅ ከመጸዳጃ ቤቱ መቀመጫ አካባቢ ባይነካካ መልካም ነው፡፡
ሁሉም ሠው የተጠቀመበትን መጸዳጃ ቤት አስተካክሎና ለሚቀጥለው ሰው ዝግጁ አድርጎ ቢወጣ የሚቆለፉ መጸዳጃ ቤቶቸንም ቁጥር ይቀንስ ነበር እንደ ሀገርም ወርቅ በመስታወት ተሰጥቶ የሚሽጥባት መጸዳጃ ቤት የሚቆለፍባት የሚለውን ጉራማይሌ ቅጥያ ያስቀርልን ነበር፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡

 አሁን ይህ መጸዳጃ ቤት ነው ወይስ መጋዘን? አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት

ሥልጣኔ በንጽሕና ይገለጻል!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may also like

No announcement available or all announcement expired.