የሚቀቀል ላስቲክ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች / Plastic and Health

 በፋሲል ፀጋዬ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በላስቲክ ተሸፋፍኖ እየተቀቀለ ለሽያጭ የሚቀርብ በቆሎ፣ ድንች፣ ስኳር ድንች የመሳሰሉ ምግቦች ማየት የተለመደ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለአብዛኛው ነዋሪ የብርድ ማባረሪያ ከመሆኑም በላይ ለበርካታ ቤተሠብ ማስተዳደሪ የዕላት ጉርስ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም እንዴት እንደሚቀቀል የሚያስተውል ሰው ያለ አይመስለነንም፡፡

በቆሎና ድንች በየመንገዱ ታፍኖ የሚቀቀልበት እንደሁም ትኩስ እንጅራ በየቤቱ የሚሸፈንበት ላስቲክ ለአብዛኛው አቅራቢና ተመጋቢ ምንም የሚያስጨንቀው አይመስለም፡፡ እንዲያውም ምግቡን ከአቧራ ተከላክሎ ትኩስ እነደሆነ ለማቆየት የተሸለ ዘዴ የተገኘ ይመስል በየአካባቢው እየተስፋፋ ነው፡፡

እነደነዚህ ዓይነት ላስቲኮች ከራሱ ከላስቲኩ ባህርይና በምርት ሂደት ውስጥ ላስቲኩን የበለጠ ለስላሳና ተጣጣፊ ለማድረግ በሚጨመሩ ኬሚካሎች ምክንያት ለጤና እጅግ አደገኛ ነው፡፡

እነዚህ ላስቲኮች የተፈጥሮ የሠውነት ቅመማትን ግራ በማጋባት የወንድ ልጅ ባህርያትን ሴታ ሴት ከማድረግ ጀምሮ አደገኛ ለሆኑ የካንሰር ዓይነቶች መንስኤ በመሆን በህዝብ ጤና ላይ የከፋ ጉዳት ያስከትላል፡፡

መጀመሪያውኑ እነዚህ ላስቲኮች ምግብ ነክ ላልሆኑ ቁሳቁሶች ማሸጊያነት ታስበው የተመረቱ በመሆናቸው እንኳንስ ምግብ በቀጥታ ታፍኖ ሊቀቀልባቸው ይቅርና ከምግብ ጋር ንክኪ ይኖራቸዋል ተብሎ አይታሰብም አይፈቀድምም ነበር፡፡ አሁን በየጎዳናው በዘፈቀደ የምንጠቀምባቸው ላስቲኮች ምን ታሽጎባቸው ወደ ህብረተሰቡ እንደደረሱ ስናስብ ደግሞ ነገሩን የበለጠ የተወሳሰበና አስደንጋጭ ያደርገዋል፡፡ በአብዘኛው የተለያዩ የማዳበሪያ ውጤቶች፣ መርዛማ ኬሚካሎች፤ የደረቅ እጠበት አገልግሎት/ላውንደሪ፣ ግንባታ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ደግሞ አደገኛ የሆኑ ቀለሞች በተለም ኳርትዝ ተብሎ የሚጠራውን የግድግዳ ቀለም ይዘው የሚመጡ ናቸው፡፡   

ላስቲክ ለሙቀት ሲጋለጥ ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ማሰብ ለሚችል ሠው ሁሉ ግልጽ ነው፡፡ በዓይን በሚታይ መልኩ አለመቅለጡ ብቻ ሳይሆን ቀስ በቀስ በውሥጡ የያዘውን ኬሚካል ወደምግቡ ይለቃዋል፡፡ ላስቲክ ለቅዝቃዜም ሆነ ለሙቀት ሲጋለጥ ደግሞ ወደ ያዘው ምግብ የተለያዩ ኬሚካሎችን እንደሚለቅ ከታወቀ ረጅም ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን እየበዛ የመጣው አጠቃላይ የጤና መጓደልና የካንሰር ችግር እነደነዚህ ዓይነት በዘፈቀደ የሚፈጸሙ ጥቃቅን የሚመስሉ ስህተቶች ጭምር ውጤት ነው፡፡

ትውልድን የሚያበላሹና የህዝብን ጤና የሚጎዱ ተግባራት የአፍሪካ መዲና በምንላት የዲፕሎማሲና የባህል ማእከል በሆነችው አዲስ አበባችን  በአደባባይ ሲፈጸሙ ማየት ደግሞ ያላዋቂነታቸን መጠንና የኋላቀርነታችንን ርቀት ያሳብቅብናል፡፡

 ስልጣኔ ማለት የሚያደርጉትን ነገር ሁሉና ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ አስቀድሞ መገንዘብና ውሳኔዎችን በሙሉ በመረጃ ላይ የተመሠረቱ ማድረግ እንጂ የፈረንጅን አፍ ኮርጆ ግራ መጋባት አይመስለኝም፡፡ እንኳንስ አሁን እጅግ ስግብገብ በሆነው ካፒታሊስት ሥርዓአተ ማህበር፣ ዓለም በተዘፈቀችበት ዘመን ሆነን ይቅርና የሠው ሥራ እንደፈጣሪ ስራ ፍፁምና ለሁሉም ተስማሚ ሆኖ አያውቅም፡፡ ሁሉንም ነገር በአንክሮ ልንመረምርና በጥበብ ልንኖር ግድ ይለናል፡፡ የፋብሪካ ውጤቶች ይነስ/ይብዛ እንጅ የጎንዮሽ ጉዳት አላቸው፡፡ በተለይ ላስቲክ ቢጣልም፣ በቀጥታ እነደገና ጥቅም ላይ ቢውልም፣ ቢቃጠልም፣ ቢቀበርም በአካባቢ፣ በእንሥሣትና በሰው ልጆች ጤና ብሎም ህልውና ላይ የከፋ ጉዳት ያስከትላል፡፡ 

ጤና ይሥጥልኝ !

ስለ ጤና፣ የስራላይ ድህንነተና አካባቢ ጉዳዮች የበለጠ ለማንብበ በድረ ገጻቸንን www.https://nitsuhethiopia.net/ ይከታተሉን፣ እነዲሁም የሚከተለውን ድረ ገጽ ይመልከቱ፡፡ https://www.health.thesfile.com/environmental-risks/environmental-toxins/plastic/

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

You may also like

No announcement available or all announcement expired.